Thursday, June 23, 2016

መጽሐፈ ምስጢር 3÷46




ይህንን መጽሐፍ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጽፎታል፡፡በእውነት የመናፍቃንን የኑፋቄ ትምሕርት ሰባብሮ የሚጥል እና እውነተኛዋን የኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ትምህርትን ግን ጥልቅ በሆነ ምስጢር የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንን ያልተረዱ መናፍቃን ለምሳሌ ቅብዓቶች ግን የመጽሐፉን  ክፍል ሙሉ በሙሉ ሣያነቡ እነሱ የሚፈልጓትን ቃል ብቻ በመውሰድ ለኑፋቄያቸው እንደ ማስረጃ ለመጥቀስ ይሞክራሉ እውነታው ግን እነሱ እንደሚሉት አይደለም፡፡ ለምሳሌ “ወልደ አብ” በተባለው የኑፋቄ መጽሐፍ ውስጥ አንድ የሚገርም አላዋቂ የጻፈው ምንባብ አግኝቸ ያንን ከየት አመጣችሁት ብየ ብጠይቅ አቶ ታደሰ መጽሐፈ ምስጢር 3÷46 አንብበው አለኝ እኔም አነበብኩት፡፡ ሳነበው ግን እርሱ የሚለውን ሃሳብ የሚደግፍ አይደለም ሊደግፍም አይችልም፡፡ ቃሉን ልጻፍላችሁ እና እናንተ ፍረዱት  “ወልደ አብ” እንዲህ ይላል የጌታችንን ልደት ሲገልጽ “እምቅድመ ዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል፣ ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን፣ ዳግም ከእመቤታችን በስጋ ተወለደ እንላለን” የተጠየቁት ጥያቄም “በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ” የሚለውን ከየት አገኛችሁት የሚል ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር  መጽሐፈ ምስጢር 3÷46” ን አንብበው ያለኝ፡፡ ምንም እንኳ የጠቀሰው መጽሐፍ እሱ ያለውን ነገር እናደማያስረዳ ባውቅም መጽሐፉን ገን አነበብኩት እንዲህም ይላል፡፡ እኔ ግን ማንበብ የጀመርኩት መጽሐፉ ማውጫ ላይ ካለው አርእስት ጀምሬ ነው፡፡ አርእስቱ በምእራፉ የተዘረዘረው ሃሳብ ምን እንደሆነ ጠቅለል አድርጎ በአጭር ቃል የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ማውጫው ላይ ያለው አርእስት እንዲህ ይላል “በእንተ ግዘተ አርዮስ” ትርጉሙም “ስለ አርዮስ ግዘት (ውግዘት)” እንግዲህ ከአርእስቱ እንደምንረዳው ይህ ምዕራፍ በዝርዝር የሚያስረዳው ወልደ አምላክን “ወልድ ፍጡር” እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ደግሞ “ወላዲተ ሰብእ” ብሎ የኑፋቄ ትምሕርት ወይም ክህደት ያስተማረውን የአርዮስን ማንነት እና የክህደት መርዙ በማውጣት አርዮስ ያለው ነገር ሁሉ ከእውነት የራቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ቃሉም እንዲህ ይላል፡፡
“ነገርነኬ በእንተ ህላዌ መለኮቱ ወትስብእቱ እምድኅረ ስጋዌሁ ኢንቤሎ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወወልደ እጓለእመሕያው በትስብእቱ”ትርጉሙም “ስለመለኮቱ እና ስለ ትስብእት ህልውና እነሆ ተናገርን ሰው ከመሆኑ በኋላ በመለኮቱ የእግዚአብሔር ልጅ በሰውነቱም የሰው ልጅ አንለውም” ይህ ቃል የሚያስረዳን  ነገር ቅድመ ተዋህዶ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ የነበሩ መለኮት እና ስጋ ከተዋሃዱ በኋላ ማለትም በተዋኅዶ የመለኮት ገንዘብ ለስጋ፣ የስጋ ገንዘብ(ከኃጢአት በስተቀር) ለመለኮት ከሆነ በኋላ፤ ሁለትነት ጠፍቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ፤ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ከሆነ በኋላ ስጋ እና መለኮትን ለያይተን በመለኮቱ የአብ ልጅ በሰውነቱ ደግሞ የሰው ልጅ ማለት እንደማይገባ ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ “ድንግልኒ ወለደት ዘኢዚአሃ መለኮተ በዘዚአሃ ስጋ ምስለ ዘዚአሃ ስጋዌ”  ትርጉሙም “ድንግልም ለእርሷ በተገባ ስጋዌ የእርሷ በሆነ ስጋ የእርሷ ያልሆነውን መለኮትን ወለደችው” ይላል፡፡ እዚህ ላይ የሚያስረዳን ነገር  ድንግል ማርያም አርዮስ በክህደቱ እንደተናገረው “ወላዲተ ሰብእ” ሳትሆን “ወላዲተ አምላክ” እንደሆነች ሲያጠይቅ “ድንግልኒ ወለደት ዘኢዚአሃ መለኮተ በዘዚአሃ ስጋ” የእርሷ ያልሆነውን መለኮት የእርሷ በሆነ ስጋ ወለደችው በማለት ገልጾታል፡፡ ቅብዓቶች እንደ ማስረጃ ሊጠቅሷት የፈለጉ ከዚህ በኋላ ያለችትን ቃል ነው፡፡ ነገር ግን ፈጽሞ ወልደ አብ ላይ ከተጻፈው ጋር አይመሳሰልም፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል “አብኒ ወለደ ዘኢዚአሁ ስጋ በዘዚአሁ መለኮት ምስለ ዘዚአሁ ኃይል ዘህሉና አምላክ” ትርጉሙም “አብም የባሕርይው ያልሆነውን ስጋ የባሕርዩ ከሆነ የህሉና አምላክ ኃይል ጋር የእርሱ በሆነ መለኮት ወለደ” እዚህ ላይ ያለው ቃል የሚያስረዳን ነገር ከተዋሕዶ በኋላ ስጋ በተዋህዶ የመለኮትን(የወልድን) ገንዘብ ገንዘቡ ስላደረገና በስጋ እና በመለኮት መካከል መለያየት ስለሌለባቸው ስግው ቃል በቀድሞው ስሙ በቀድሞው ግብሩ እና በቀድሞው ህላዌው ስለጸና ማለትም ስግው ቃል (ስጋን የተዋሃደ) መለኮት ወልደ አብ፣ ኃያል አምላክ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ፣ ከአብ አና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለ፣ እንዲሁም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በህልውና የሚገናዘብ ሆነ ማለት ነው፡፡ቅድመ ተዋህዶ ወልደ አብ ይባል የነበረ ወልድ ድኅረ ተዋህዶም ወልደ አብ በሚባል በጥንት ግብሩ ጸና፤ ወልደ አብ መባልን ገንዘቡ አደረገ እንጅ አርዮስ እና ሌሎቹ መናፍቃን እንደሚሉት ወልድ  ፍጡር አይባልም ለማለት ነው ስለዚህ ምስጢሩን ሳንረዳ ወደ ተሳሳተ መንገድ መሄድ እንደሌለብን አባቶቻችን አስተምረዋል አሁንም እያስተማሩ ነው፡፡ በሀይማኖተ አበውም ስለልደቱ ተጽፎ የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ “ዳግመኛም ለወልደ እግዚአብሔር ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምን ዘንድ ይገባናል፡፡ አንዱ ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ነው፡፡ ሁለተኛው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን የተወለደው ነው፡፡” ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ 34÷6 ስለዚህ አባቶቻችን ባስተማሩን ትምህርት መጽናት ያስፈልጋል፡፡

No comments:

Post a Comment